አጠቃላይ
ለእውነት እንታዘዝ
ወደ ገላትያ 3:1-5
የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው? ይህን ብቻ ከእናንተ እንድማር እወዳለሁ፤ በሕግ ሥራ ወይም ከእምነት ጋር በሆነ መስማት መንፈስን ተቀበላችሁን? እንዲህን የማታስተውሉ ናችሁ? በመንፈስ ጀምራችሁ አሁን በሥጋ ትፈጸማላችሁን? በውኑ ከንቱ እንደ ሆነስ እንደዚህ ያለ መከራ በከንቱ ተቀበላችሁን? እንግዲህ መንፈስን የሚሰጣችሁ በእናንተም ዘንድ ተአምራት የሚያደርግ፥ በሕግ ሥራ ነውን ወይስ ከእምነት ጋር በሆነ መስማት ነው?
የገላትያ ሰዎች እየሱስ በፊታቸው እንደተሰቀለ ያህል ነበር ወንጌል የገባቸው የነበረው ሐሰተኛ አስተማሪዎች ገብተው ዓይናቸውን ከመስቀሉ ላይ እስኪያስነሷቸው ድረስ:: ይህ ሲሆን ግን አላስተዋሉም ለእውነት መታዘዝ ማቆማቸውን:: በህግ ሳይሆን በእምነት ነበር የመንፈስ ቅዱስን ስራ ሁሉ ያዩትና የተለማመዱት የነበረው:: ዛሬ ታድያ ምን ተፈጠረ በመንፈስ ጀምራችሁ በስጋ የምትፈጽሙት እያለ ነው አወዳደቃቸውን የሚያሳያቸው::
ወደኛ ስንመለስ ይህ ሁሉ ለትምህርታችን ነውና እንዴት እንገኛለን? በእምነት ወይስ በስጋ አስተሳሰብ? እዚህጋ የህግን ስራ የስጋ ነገር እንደሆነ ጳውሎስ እያቀያየረ ይጠቀምበታል:: ለስጋውያን መንፈሳዊ ነገር ሞኝነት ነው ለእኛ ግን መንፈሳውያን ለሆንን ህይወት ነው:: ስንቶቹን አገልጋዮችን በዚህ ምክንያት አተን ይሆን? መንፈስ ቅዱስ በህይወታችን የሚሰራው በእምነት እንጂ በስራ አይደለምና እንንቃ:: ስለዚህ የመስቀሉን ስራ በማመንና ዓይናችንን በርሱ ላይ በማድረግ ይበቃናል:: ደህንነታችን አይቅለልብን የእየሱስን ህይወት አስከፍሏልና በእምነት እንጏዝ:: የጌታ ጸጋ ይብዛልን!
________________
በእምነት መጽደቅ
ወደ ገላትያ 3: 6-9
እንዲሁ አብርሃም በእግዚአብሔር አመነና ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት።
እንኪያስ ከእምነት የሆኑት እነዚህ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ እወቁ። መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ፡— በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ፡ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ። እንደዚህ ከእምነት የሆኑት ካመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ።
የሚገርመው አብርሐም የብሉይ ኪዳን ሰው ሆኖ ሳለ ወንጌል ደርሶት አምኖ ነበር:: አይገርምም?! እየሱስ እኮ ገና አልመጣም፤ አላየውም፤ አልተጻፈለት እንደኛ ግን በእግዚአብሔር አመነና ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት። እኛ ግን ዛሬ በዛ ኪዳን ውስጥ እያለን ሌላ ያስመኘናል እሱም የህግ ባርነት!
አይሁድ እኛ የአብርሃም ልጆች ነን ብለው ሲሉ የነበረው ለእየሱስ ይህን ማለታቸው ነው:: ለማንም አልተገዛንም ብለው የሚመኩት:: ግን የህይወትን ራስ አብርሐም ከሩቅ አይቶ ያመነውን ጌታ ማየት አልቻሉም አጠገባቸው ሲመላለስ አላወቁትም ስለዚህም አሳልፈው ሰጡት::
ለእኛ ግን ለምናምን የአብርሃም በረከት በክርስቶስ ደረሰን እናም ''በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ፡'' የተባለው ደረሰንና ዛሬ እየኖርንበት ነው::
ስለዚህ አሁን ቃሉ እንደሚል ''እንደዚህ ከእምነት የሆኑት ካመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ። '' ይለናል እኛም አሜን እንላለን!
___________________
ጻድቅ በእምነት ይኖራል
ወደ ገላትያ 3:10-12
ከሕግ ሥራ የሆኑት ሁሉ በእርግማን በታች ናቸውና፤ በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ሁሉ ጸንቶ የማይኖር የማያደርግም ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና። ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎአልና ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንዳይጸድቅ ግልጥ ነው። ሕግም ከእምነት አይደለም፡ ነገር ግን፡— የሚያደርገው ይኖርበታል፡ ተብሎአል።
ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎ ሲባል አታነክሱ እያለ ነው ጳውሎስ ከእምነት ወይም ከህግ አንዱን ምረጡ እንጂ ሁሉቱንም ይዞ መሄድ አይቻልም ብሎ ሲያበቃ ፍጻሜውንም ያሳየናል:: ህግን ከተከትልን በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ሁሉ ጸንቶ የማይኖር የማያደርግም ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ኑሮአችን ከእርግማን በታች መሆን ነው ማለት ነው:: በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንዳይጸድቅ ግልጥ ነው። ማንም መፈጸም ስላልቻለ አይደል እንዴ ጌታ የመጣው?! ስለዚህ ፊታችንን ወደ እምነት እናዙር ጠላት አብዝቶ ፊታችንን ወደ ሚከለክልበት አቅጣጫ ማለት ነው:: ከእምነት ስንርቅ ለጠላት ቀላል ኢላማው ነን የማያልቅ የቤት ስራ ሲያሰራን ይኖራል ያልበቃን እንደሆንን ሁልጊዜ በማሳየት:: ዛሬም ነገም እየተመላለስን ማሳረም ነው ማለት ነው ስራችን ፈተናው 'open book’ ሆኖ ሁሉም ይለፍ በክርስቶስ በኩል ተብሎ እያለ እኛ ግን ጊዜና ጉልበት ለማያስፈልግ ነገር እያባከንን እንዳንገኝ ብቻ:: እንንቃ!!!!
ጎበዝ እንንቃ የተባልነው እኮ ጻድቅ በእምነት ይኖራል እንጂ በስራ አይደለም:: መቼም ይህን ብዬ ስል እንደው እንደፈለግን በሐጥያት እንመላለስ ማለቴ እንዳልሆነ ይሰመርበት እንደዛማ ከሆነ ጭርሱን በደህንነት ሰፈርም አላለፍን ማለት ነው ክርስቶስን መምሰል ግድ ይላል:: በአእምሯችን መታደስ እንለወጥ እንጂ የሆነ ነገር achieve ለማድረግ አንጣር እንረጋጋ እዳችን ተሰርዟል ነጻ ነን ማመን ነው የሚጠበቅብን:: እግዚአብሔር መዳንን ቀላል ስላደረገው የዚህ ዓለም ጥበበኞች ከበዳቸው:: እኛ ግን መዳን በእምነት እንደሆነ ገብቶናል:: አናሻሽለውም አሜን እንጂ! እየሱስ ከህግ እርግማን ዋጅቶናል!! አሜን!
______________________
ከሕግ እርግማን ክርስቶስ ዋጀን
ወደ ገላትያ 3: 13-14
በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤ የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል፥ የአብርሃም በረከት ወደ አሕዛብ በኢየሱስ ክርስቶስ ይደርስላቸው ዘንድ።
ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤ እርሱ ራሱን የሰጠው እና የተንገላታው እኛ ከዚህ የሕግ እርግማን ነፃ እንድንሆን ነው:: እርሱ ሐጥያትን የማያውቅ ንፁ ሆኖ ሳለ በእንጨት ላይ በተሰቀለ ጊዜ ግን እርሱም እርግማን ሆኖ ከእኛ ጋር ተካፍሎ ነፃ አወጣን:: ሃሌሉያ! አሜን!
ሕግ የመጣው የእግዚአብሔርን የቅድስና ልክና ከእኛ የሚጠበቀውን ሊያሳየንና አዳኝ እንደሚያስፈልገን ለማሳየት ነው:: ከዚህ በፊት እንዳልኩት ሕግ የተሾመበት ስራው እየተከታተለ ስህተትን ማሳየት ነው እሱንም በትጋት ሰርቷል::
ሕግ የመጣው በሙሴ ነው የመጣውም ለእስራኤላውያን እንጂ ለኔ ለአሕዛብዋ አይደለም:: እኔ ግን እንደአሕዛብ የእግዚአብሔርን የቅድስና ልክ (standard) መድረስ ስላልቻልኩ ከቁጣ በታች ተዘግቶብኝ ነበር:: አብርሐም የኖረው ከሕግ በፊት ነበር:: ስለዚህም አብርሐም ወንጌል ተሰበከለት እርሱም ተቀበለና ጽድቅ ሆኖ የተቆጠረለት:: የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል፥ እኔም ይህንን የመዳን ወንጌል ስቀበል በእምነት የአብርሀም በረከት በእየሱስ ክርስቶስ ለእኔ ለአሕዛብዋ ደረሰልኝ:: መድረስ ያልቻልኩትን ያንን የቅድስና ከፍታ በእየሱስ በማመን የእርሱ ጽድቅ ለኔ ተቆጥሮ ይህንን ሰማያዊ መንግስት ተቀላቀልኩኝ:: ዛሬ በስራዬ እንደማላስደስተው ያወኩኝ በጸጋው የዳንኩኝ ልጅ ነኝ:: አሜን!
_________________
በተስፋ ቃል እግዚአብሔር ርስት ሰጥቶአል
ወደ ገላትያ 3: 15-20
ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። የሰው ስንኳ ቢሆን እርግጠኛውን ኪዳን ማንም አይንቅም ወይም አይጨምርበትም። ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ። ስለ ብዙዎች እንደሚነገር፡— ለዘሮቹም፡ አይልም፤ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን፡— ለዘርህም፡ ይላል፥ እርሱም ክርስቶስ። ይህንም እላለሁ፤ ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የተሰጠው ሕግ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተረጋገጠውን ኪዳን የተስፋውን ቃል እስኪሽር ድረስ አያፈርስም። ርስቱ በሕግ ቢሆንስ እንግዲያስ በተስፋ ቃል አይሆንም፤ በተስፋ ቃል ግን እግዚአብሔር ለአብርሃም ሰጥቶአል። እንግዲህ ሕግ ምንድር ነው? ተስፋው የተሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ በመካከለኛ እጅ በመላእክት በኩል ስለ ሕግ መተላለፍ ተጨመረ። መካከለኛውም ለአንድ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር ግን አንድ ነው።
ሕግ ምንድር ነው? መልሱ:-
ተስፋው የተሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ በመካከለኛ እጅ በመላእክት በኩል ስለ ሕግ መተላለፍ ተጨመረ:: ስለዚህ ሕግ መዳረሻ ነው ማለትም ዘሩ እስኪመጣ::
ይህ ዘር ማነው?
ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ። ስለ ብዙዎች እንደሚነገር፡— ለዘሮቹም፡ አይልም፤ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን፡— ለዘርህም፡ ይላል፥ እርሱም ክርስቶስ። አሜን ሕግ ስራው ጨርሶ ተሰናብቷል የተጠበቀው ስለመጣ እርሱም ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መካከለኛው አምላክ ብቻ ሳይሆን እንደ እኛው ሰው ሆኖ የኖረው:: የአብርሃም ዘር የሆነው ክርስቶስ መቷል:: ስለዚህም ቃሉ እንደሚል መካከለኛውም ለአንድ ብቻ አይደለም ለሰው ብቻ አይደለም ወይም ለእግዚአብሔር ፤ ነገር ግን ሁለቱንም ያማከለ መካከለኛ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል አለ፤ ሁለቱን ያስታረቀ፤ የጥልን ግድግዳ ያፈረሰ፤ ዛሬም የሚማልድ ሊቀ ካህን የሆነው እየሱስ ክርስቶስ አለልን በሰማይ:: አሜን!
ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የተሰጠው ሕግ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተረጋገጠውን ኪዳን የተስፋውን ቃል እስኪሽር ድረስ አያፈርስም።ርስቱ በሕግ ቢሆንስ እንግዲያስ በተስፋ ቃል አይሆንም፤ በተስፋ ቃል ግን እግዚአብሔር ለአብርሃም ሰጥቶአል። የሰው ስንኳ ቢሆን እርግጠኛውን ኪዳን ማንም አይንቅም ወይም አይጨምርበትም።
ስለዚህ አሮጌው የሕግ ስርዓት ተሽሯል እናም ዕርስታችንን የምንወርሰው በሕግ ሳይሆን በተስፋ ቃል ነው ያም የተስፋ ቃል ለአብርሃም ተስቷል ለእኛም ለምናምን ዛሬ በክርስቶስ በዘሩ በኩል ደርሶልናል:: አሜን!
Like