Day 1. በሐሰተኞች አለመነዳት
ወደ ገላትያ 2: 1-10
ከዚህ በፊት እንዳየነው ጳውሎስ መልእክቱ ለገላትያ ሰዎች ወንጌል ብቻውን ነው የሚያድነው እንጂ ካልተገረዛችሁና የሙሴን ህግ ካልጠበቃችሁ የሚሉትን አትስሙ ነው የሚለው እዚህም ክፍል ላይ ምክንያቱን እንይ::
ከ14 ዓመት በኋላ ከበርናባስ ጋር ቲቶን ደግሞ ይዤ ወደ ኢየሩሳሌም ሁለተኛ ወጣሁ፤ (መጀመሪያ ሄዶ የነበረው ከዳነ ከ3 ዓመት በኃላ እንደነበር አይተናል)
እንደ ተገለጠልኝም ወጣሁ፤ ምናልባትም በከንቱ እንዳልሮጥ ወይም በከንቱ ሮጬ እንዳልሆን በአሕዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል አስታወቅኋቸው፤ ዋኖች ግን መስለው ለሚታዩ ለብቻቸው አስታወቅኋቸው። ነገር ግን ከእኔ ጋር የነበረ ቲቶ እንኳ የግሪክ ሰው ሲሆን ይገረዝ ዘንድ ግድ አላሉትም፤
ለምን አህዛብ የሆነውን ቲቶን ይዞ ሄደ? ስለመገረዝ አንድ እልባት ለመስጠት ፈልጎ ነው:: ታሪኩን በሐዋርያት ስራ 15 ላይ እናገኘዋለን:: መሪዎቹ አላስገደዱትም እንዲገረዝ:: አትሳቱ አያስፈልግም እያላቸው ነው::
ነገር ግን ባሪያዎች ሊያደርጉን በክርስቶስ ኢየሱስ ያለንን አርነታችንን ይሰልሉ ዘንድ ሾልከው በስውር ስለ ገቡ ስለ ሐሰተኞች ወንድሞች ነበረ።
ጳውሎስ ጠንቅቆ ያውቅ ነበር ሾልከው የገቡ ሐሰተኛ ወንድሞች ይህንን እንዳደረጉ::ስለዚህ መሪዎች የሆኑትም እጃቸውን ሰጡኝ ቀጥል ብለው እንጂ አልተቃወሙኝም እያለ ነው::
ጴጥሮስ ለተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠው እንዲሁ ለእኔ ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠኝ አዩ፤ ለተገረዙት ሐዋርያ እንዲሆን ለጴጥሮስ የሠራለት፥ ለእኔ ደግሞ ለአሕዛብ ሐዋርያ እንድሆን ሠርቶአልና። ደግሞ የተሰጠኝን ጸጋ አውቀው፥ አዕማድ መስለው የሚታዩ ያዕቆብና ኬፋ ዮሐንስም እኛ ወደ አሕዛብ እነርሱም ወደ ተገረዙት ይሄዱ ዘንድ ለእኔና ለበርናባስ ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤ ድሆችን እናስብ ዘንድ ብቻ ለመኑን፥ ይህንም ደግሞ ላደርግ ተጋሁ።
የሰጡት ትዕዛዝ አንድ ነው የሙሴን ህግ መጠበቅ ወይም መገረዝ ሳይሆን እነዚህ ከውጪ የሚደረጉ ነገሮች ናቸውና የውስጥ የሆነውን የፍቅርን አገልግሎት እሱም ደሆችን ማሰብ::
ለእኛም ይህ ነው የጌታ ትዕዛዝ በሄድንበት ሁሉ ደሀን እናስብ እናም አርነታችንን አናስነጥቅ::
Day 2.
ለእውነት እንቁም
ወደ ገላትያ 2: 11-14
ነገር ግን ኬፋ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ ፊት ለፊት ተቃወምሁት፥ ይፈረድበት ዘንድ ይገባ ነበርና። አንዳንድ ከያዕቆብ ዘንድ ሳይመጡ ከአሕዛብ ጋር አብሮ ይበላ ነበርና፤ በመጡ ጊዜ ግን ከተገረዙት ወገን ያሉትን ፈርቶ ያፈገፍግ ነበርና ከእነርሱ ተለየ። የቀሩትም አይሁድ ደግሞ፥ በርናባስ ስንኳ በግብዝነታቸው እስከ ተሳበ ድረስ፥ ከእርሱ ጋር አብረው ግብዞች ሆኑ። ነገር ግን እንደ ወንጌል እውነት በቅንነት እንዳልሄዱ ባየሁ ጊዜ በሁሉ ፊት ኬፋን፡— አንተ አይሁዳዊ ሳለህ በአይሁድ ኑሮ ያይደለ በአሕዛብ ኑሮ ብትኖር፥ አሕዛብ በአይሁድ ኑሮ ሊኖሩ እንዴት ግድ አልሃቸው? አልሁት።
እዚህጋ የምንመለከተው ጴጥሮስ አንጾኪያ ያለችውን ቤተክርስቲያን ሊጎበኝ መቶ እያለ ስለተፈጠረው ነገር ነው የሚነግረን:: ጴጥሮስ ከእየሩሳሌም ወገኖች ሳይመጡ በፊት ከአህዛብ ጋር ይበላ ነበር ሰዎቹ ከመጡ በኃላ ግን ማስመሰል ጀመረ እንደማይበላና የሙሴን ህግ እንደሚጠብቅ:: በዚህ ጊዜ ነበር ጳውሎስ ትናንት ሌላ ዛሬ ሌላ ሲሆንበት በሁሉ ፊት የወቀሰው:: የጥልን ግድግዳ አፍርሷል ብለን ታድያ እንዴት መስበክ ይቻላል? እየሱስ እኮ ቀርበው ላሉትም ሰላምን ርቀን ላለነውም ሰላምን ነው የሰበከውና አንድ ጊዜ የጥልን ግድግዳ አፍርሶ በሰማይና በምድር ያለውን ከአባቱ ጋር ያስታረቀው:: ሊወቀስ ይገባው ነበር ጴጥሮስ እንደመሪ ይህንን ሲያይ እንደዚህ እነዚያን ሲያይ እንደዛ መሆን አልነበረበትም ባይ ነው ጳውሎስ:: እንደዚህ ደግሞ መኖር ከፈለክ አህዛብም እንደራሳቸው ህግ ይኑርዋ የእኛን ህግ አንጫንባቸው ነው የሚለው ይሄ ግን ወጥ የክርስቶስ አካል አያደርጋትም ስለዚህ ወደ አንዱ እንምጣ ሁሉ አንድ ነው መለያየት የለም::
ስለዚህ የተማርኩት ነገር ለገባኝ እውነት በየትኛውም አጋጣሚ ጸንቶ መኖር እናም ህያው የወንጌል ምስክር መሆን አለብኝ::
Day 3.
በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ጸድቀናል
ወደ ገላትያ 2: 15-16
እኛ በፍጥረት አይሁድ ነን ኃጢአተኞችም የሆኑ አሕዛብ አይደለንም፤ ነገር ግን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ እንዳይሆን አውቀን፥ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ፥ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል።
1. እኛ በፍጥረት አይሁድ ነን
ኃጢአተኞችም የሆኑ አሕዛብ
አይደለንም፤
የሚገርመው ነገር ከአይሁድ ውጪ ያለውን ሰው ሁሉ አይሁዶች ሐጥያተኛ ብለው ነው የሚጠሩት:: ለዚህም ነው እዚህጋ ጳውሎስ ትምክህት ቢያስፈልግ አለኝ አይሁድ ነኝ እንጂ አህዛብ አይደለሁም ይልና ሲቀጥል ያፈርሰዋል ምንም እንደማይጠቅም::
2. ነገር ግን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ
በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ
ሥራ እንዳይሆን አውቀን፥ ሥጋን
የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ
ስለማይጸድቅ፥
የምንጸድቀው በአንድና አንድ ነገር በማመን ብቻ ነው እርሱም በክርስቶስ እንጂ የህግንማ ስራ እኛም ትተነዋል የሙሴን ህግማ በመጠበቅ የሚዳን ቢሆንማ እኮ የሚጠብቅ ነበረ ግን ህግ ከመክሰስ ያለፈ የማጽደቅን ስራ አይሰራም:: እየተከታተለ ስራውን ይሰራ ነበር በትጋት እሱም መክሰሱን ያለ ርህራሄ እዚህ ጋር ልለፍ ቀላል ነገር ነው የተሰራውወይም ትላንትና በርትቶ ነበር ብሎ እንኳን ግንዛቤ ውስጥ የሚያስገባው ነገር የለም ስለዚህ እግዚአብሔር እርሱን አሮጌ አድርጎ አዲስን መንገድ ከፈተልን ሁሉን እኩል አድርጎ በጸጋ የሰውን ልጅ ሁሉ አጸደቀ:: አሜን!
3. እኛ ራሳችን በሕግ
ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት
እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል።
ስለዚህ ያመነው በጽድቅ ስራ ሳይሆን በክርስቶድ ነው ያንን መንገድ በደንብ ሄጄበታለሁ አድካሚ ነው የሚሻለው አሁን ያስተዋወኳችሁን እውነት መያዝ ነው እሱም በክርስቶስ ኢየሱስ አምኖ መዳን::
ጌታ ይርዳን በጸጋ ጀምረን የህግ ምሁራን እንዳንሆን አይናችንና ልባችን ሁልጊዜ በጸጋው ላይ ይሁን አንቀላቅል ለዚህ ነው ዕለት ዕለት እራሳችንን መስበክና ማንቃት ያለብን ድንገት እህግ ሰፈር እንዳንገኝ አስተሳሰባችንን ሁሉ እንለውጥ ከተመካንም በእየሱስ ስራ ላይ ብቻ ይሁን::
Day 4.
ለእግዚአብሔር ሕያው ሆኜ እኖራለሁ
ወደ ገላትያ 2: 17-19
ነገር ግን በክርስቶስ ልንጸድቅ የምንፈልግ ስንሆን ራሳችን ደግሞ ኃጢአተኞች ሆነን ከተገኘን፥ እንግዲያስ ክርስቶስ የኃጢአት አገልጋይ ነዋ? አይደለም። ያፈረስሁትን ይህን እንደ ገና የማንጽ ከሆንሁ ራሴ ሕግ ተላላፊ እንድሆን አስረዳለሁና። እኔ ለእግዚአብሔር ሕያው ሆኜ እኖር ዘንድ በሕግ በኩል ለሕግ ሞቼ ነበርና።
በክርስቶስ የጸደቅን እኛ በጸጋ ድነናል ብለን ስንል እኮ ሐጥያትን ለማድረግ ላይሰንስ አግኝተናል ለማለት አይደለም:: እንዲያውም የህይወት አኗኗራችን ደረጃው ጨምሯል እያልን ነው:: እኛ የጽድቅ አገልጋዮች ነን:: ቃሉ በሌላ ስፍራም እንደሚል ''ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፥ ዘሩ በእርሱ ይኖራልና፤ ከእግዚአብሔርም ተወልዶአልና ኃጢአትን ሊያደርግ አይችልም።'' በክርስቶስ ያገኘነው ማንነት ይሄ ነው የጽድቅ ዘር በእኛ አለ::
ስለዚህ ህግ እየተከታተለ አይከሰኝም የእኔ ደረጃ ከፍ ብሏል ከጸጋ እንጂ ከህግ በታች አይደለሁም:: እግዚአብሔር የዚህን ዓለም ምኞት ሁሉ የምክድበትን ጸጋ በእኔ አስቀምጧልና ብቃት አለኝ ጸጋው በዝቶልኛል የዓለም ነገር ለኔ ሞኝነት እንዲሆን አድርጏል ጸጋው::
ስለዚህ እኔ ህያው ሆኜ ለእግዚአብሔር እኖራለሁ እንጂ ለህግማ ሞቻለሁ:: የሞተ ይነሳል እንዴ?! አረ በፍጹም! ለህግ አልነሳም ያለሁበት ተመችቶኛል ከፍታ በጌታ ጸጋ! አሜን!
ከወጣሁበት ከፍታዬ አልወርድም! የጌታ ስም ይባረክ በእኔ ውስጥ ጽድቅን ጨምሮ ከህግ የበላይ ላደረገኝ!
Day 5.
ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል
ወደ ገላትያ 2:20-21
ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው። የእግዚአብሔርን ጸጋ አልጥልም፤ ጽድቅስ በሕግ በኩል ከሆነ እንኪያስ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ።
እየሱስ አንድ ነገር አለ ዕለት ዕለት መስቀሉን ተሸክሞ የማይከተለኝ ለኔ ሊሆን አይገባውም ሲል እዚህጋ ጳውሎስም ያጠናክረዋል አሁን እየተካሄደ እንዳለ አድርጎ ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ ይላል:: መቼ? አሁን ወይም ሁልጊዜ::
መስቀል ማለት የምንገኝበት ሁኔታ/ኮንድሽን ማለት ነው እርሱም ለዓለም፤ ለራሳችንና ለሐጥያት ሞተናል:: ሕያው ሆነን የምንኖረው እኛ ሳንሆን ህይወቱን የለወጠን እየሱስ ነው በእኛ የሚኖረው:: አሜን!
ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም። እንደሚል ቃሉ መውደድና መስጠት አብረው የሚሄዱ ናቸው ወደደንና እራሱን ስለእኛ ሰጠ:: ስለዚህ ለታደገኝ ጌታ ብኖርለትና ህይወቴን ኑርበት ብዬ ፍቅሬን እኔስ በመስጠት ብገልጠው?! ይገባዋል!
እርሱ ስለእኔ እንደበግ በሸላቾቹ ፊት ዝም ብሏል ሲበዛበት ይህች ጽዋ ትለፍ አለ ግን የእኔ ሳይሆን ያንተ ፈቃድ ይሁን ብሎ ስለእኔ ራሱን ሰጠ መድህኔ:: ታድያ ብኖርለት ምን ይገርማል? እኖራለሁኝ ለእርሱ ክብር ዓለምን፤ ሐጥያትን እራሴንም ክጄዋለሁ እኔ አሁን የምኖረው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ብቻ ነው። አሜን!
የእግዚአብሔርን ጸጋ አልጥልም፤ እንዲህ ሊታደገኝ ተንገላቶ እያለ እየሱስ እናም ሕግን አላቆመውም ምክንያቱም አልችልም ሕግን ጠብቄ መጽደቅ የከፈለውንም የመስቀል ዋጋ ከንቱ አላደርግም:: ላዳነኝ በድንቅ አሰራሩ ለጠራኝ ጌታ ክብር ይሁን::