Day 1
ዛሬ የምጀምረው ክፍል ገላትያን ነው ጌታም ያስተምረናል:: ትንሽ መግቢያ የሚሆን ሀሳብ እንይና የዛሬውን ቃል እናጠናለን::
የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ጳውሎስ ነው
የሚጽፍበትም ምክንያት:-
1. ክርስትናንና አይሁዳዊነትን እየቀላቀሉ ስለነበር
2. ከእምነት በምን አይነት ፍጥንት እንደራቁ ስለተገነዘበ
3. ፀጋን/ጽድቅን ከስራ ጋር በመቀላቀላቸው
4. መዳን በፀጋ መሆኑን ሊያሳያቸው
ወደ ገላትያ 1: 1-2፤ በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታንም ባነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆነ እንጂ ከሰዎች ወይም በሰው ያልሆነ ጳውሎስ ከእኔም ጋር ያሉት ወንድሞች ሁሉ፥ ወደ ገላትያ አብያተ ክርስቲያናት፤
እዚህ ጋር ጳውሎስ ሊያሳያቸው የፈለገው ማን እንደላከው ነው:: በእግዚአብሔር ነው ሐዋርያ የሆንኩት እርሱ ነው የጠራና የላከኝ እያላችው ነው:: ለምን ብለን ስንል ባለው ስልጣን መሰረት የሚናገረውን ሁሉ ከዚህ በኃላ ከእግዚአብሔር የተላከ መልእክት አድርገው እንዲወስዱት እንጂ ይህ የጳውሎስ ሀሳብ ነው እንዳይሉ ነው::
እርሱ ብቻም አይደለም አብረውትም የሚያገለግሉ ወንድሞች ሁሉ ያመኑበትን ነገር እየጻፈላቸው እንደሆነ እየነገራቸው ነው:: ስለዚህ ብትቀበሉ ይሻላል መልክታችንን ብሎ ነው የሚላቸው::
ከዚህ የማየው ነገር;- እኔን የጠራ ጌታ እንደሆነና ዋጋ የክፈለና የራሱ ያደረገኝን ጌታን አገልግለውና ለእርሱም የምገዛ፤ ደስ የማሰኘው ልጅ መሆን ነው የእኔ ድርሻ:: ስሙ ይባረክ:: አሜን!
Day 2.
ወንጌል አንድ ነው
ወደ ገላትያ 1:7-10
እርሱ ግን ሌላ ወንጌል አይደለም፤ የሚያናውጡአችሁ የክርስቶስንም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንዶች አሉ እንጂ።
ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን።
አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።
ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን? ወይም ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም።
የተቀበልነው ወንጌል አንድ ነው እርሱም በጸጋ መዳናችን ነው:: በስራ አይደለም ደግሞም የምንጨምርበት ነገር የለም ተጠናቋል:: ስለተሻገርን መዳን ቀሎ አይታየን አንዳንዴ ለሰዎች ስትመሰክሩ ነው ከባድነቱ የሚታየው ሰው እንዴት ይሄ መዳን አይታየውም አትሉም? የዚህ ዓለም ገዢ አይምሮን ያሳውራል ያንን ሁሉ አልፈን መተን ደግሞ አሁን መወናበድ የለብንም የዳነው በጸጋ ነው የምንጨምርበት ከእንትና የተሻልኩ ነኝ የምንልበት ምንም ማማሀኛ የለም የማይገባን ነበርን ከትልቅ ምህረቱ የተነሳ ቀድሶ ወደ ራሱ አስጠጋን::
ከዚህ እውነት ውጪ ሰዎችን ለማሳመንም ሆነ ለአስተሳሰባችን እንዲመች አድርገን ቃሉን አናጣምም ቃሉ እዚህ ጋር የሚለው እንደዚህ አይነቱ የተረገመ ይሁን ነው::
ስለዚህ ከሰው ይልቅ አምላካችንንና አባታችንን ደስ ማሰኘት ይሻላል:: የምወደው ልጄ ይህ ነው በእርሱ ደስ የሚለኝ ብሎ አንድ ጊዜ በልጁ ደስ ተሰኝቷል:: የሐጥያት ዋጋ ሙሉው ተከፍሏል እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ልጁን መልበስ ነው:: እርሱ ውስጥ ወስዶ በአብ ቀኝ የሰወረንም ለዚሁ ነው ስራ አበቃ እዳ ሁሉ ተከፈለ ብሎ ደስ አለው አብ ቤተሰቡ ሁሉ ትሰብስቦ ሲያይ በልጁ ውስጥ አለቀ! ሌላ ስራ አያስፈልግም አትናወጡ ቅዱሳን!
Day 3
ወንጌል የሚገለጥ ነው
ወደ ገላትያ1: 11-12
ወንድሞች ሆይ፥ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም።
1. ወንድሞች ሆይ፥ በእኔ የተሰበከ
ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ
አስታውቃችኋለሁ፤
እኔ ከሰው ተቀብዬ አይደለም ወንጌልን የሰበኩት ከራሱ ከጠሪው ነው የተማርኩትናም የሰበኩት እያለ ነው:: መለኮታዊ ነው ጥሪዬ ድምጹን ሰምቼ፤ አይኔም ከክብሩ የተነሳ ታውሮ፤ ሰዎችን ያሳደድኩ መስሎኝ ፈጣሪዬን ሳሳድድ የነበርኩትን ራርቶ በህይወት አኖረኝና ይህንን ወንጌል ሰጠኝ እያለን ነው:: ዛሬም ጥሪ አለ፤ ዛሬም መላክ አለ፤ ዛሬም መገለጥ አለ:: ጌታ በስራ ላይ ነው::
2. ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ
እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም
አልተማርሁትምም::
ይሄ ቃል በጣም ዋጋ አለው ለእኔ ምክንያቱም ጳውሎስ ወንጌልን የተማረው ከራሱ ከእየሱስ ነው:: ወንጌል ሁልጊዜ አዲስ ነው፤ የሚሰራ ነው በሐዋርያት ብቻ ብሎ ነገር የለም:: ዛሬም ለእኔ ወንጌሉን ያበራልኝ በመንፈሱ ነው:: ጸጋ ቢሆን ዛሬ ይሰጣል፤ ቃሉን መግለጥ ቢሆን ዛሬ ይሰጣል ምክንያቱም እየሱስ በስራ ላይ ነው ሙሽራይቱን ያስውባል፤ አካሉንም አገልጋዮችን ልኮ ይገነባል:: ጳውሎስ እንዴት እንደተጠራ ሲመሰክር እንዲህ ብሏል በሐዋርያት ስራ ላይ
''ነገር ግን ተነሣና በእግርህ ቁም፤ ስለዚህ እኔን ባየህበት ነገር ለአንተም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር ትሆን ዘንድ ልሾምህ ታይቼልሃለሁና። የኃጢአትንም ስርየት በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስትን ያገኙ ዘንድ፥ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ዘወር እንዲሉ ዓይናቸውን ትከፍት ዘንድ፥ ከሕዝቡና ወደ እነርሱ ከምልክህ ከአሕዛብ አድንሃለሁ።''
ዛሬም ወንጌል አልተለወጠም ይህንን የከበረ ቃል ይዘን እንወጣለን:: አሜን
Day 4
ወንጌል በአሳዳጁ ሲሰበክ
ወደ ገላትያ 1: 13-24
ከዚህ በፊት እንዳየነው ጳውሎስ ከጌታ እንደተቀበለና እንደተማረ አይተናል:: እስኪ እንየው የእርሱ ትኩረት የነበረውን ከደማስቆ መንገድ በፊት:-
1. በአይሁድ ሥርዓት በፊት እንዴት እንደ ኖርሁ ሰምታችኋልና፤
2. የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ያለ ልክ አሳድድና አጠፋ ነበር፥
3. ለአባቶችም ወግ ከመጠን ይልቅ እየቀናሁ በወገኔ ዘንድ በዘመኔ ካሉት ብዙዎችን በአይሁድ ሥርዓት እበልጥ ነበር።
ከደማስቆ መንገድ በኃላ ደግሞ:-
1. በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ ለየኝ በጸጋውም ጠራኝ
2. እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፥
3. ከእኔም በፊት ሐዋርያት ወደ ነበሩት ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፥
4. ከዚህ ወዲያ ከሦስት ዓመት በኋላ ኬፋን ልጠይቅ ወደ ኢየሩሳሌም ወጥቼ ከእርሱ ጋር አሥራ አምስት ቀን ሰነበትሁ፤ ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በቀር ከሐዋርያት ሌላ አላየሁም።
5. ስለምፅፍላችሁም ነገር፥ እነሆ፥ በእግዚአብሔር ፊት ሐሰት አልናገርም።
6. ነገር ግን፡— ቀድሞ እኛን ያሳድድ የነበረ፥ እርሱ በፊት ያጠፋው የነበረውን ሃይማኖት አሁን ይሰብካል፡ ተብሎ ሲነገር ይሰሙ ነበር፤
ስለ እኔም እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበር።
ይህን ሁሉ ነገር የሚነግራቸው መግቢያው ላይ ለጠቀሰው ሀሳብ ማጠናከሪያ ነው:: ሐዋርያ መሆኑን በፊት ከተጠሩት ሐዋርያት እንኳን ሁለቱን ብቻ እንዳገኘ እነሱንም ያገኘው ወድያው እንዳልሆንና ለተገለጠለግ እውነት ወድያው ምላሽ ሰቶ እንዳገለገለ ነው የሚያስረግጠው ስለዚህ እኔ የነገርኳችሁ ወይም ያስተማርኳችሁ ወንጌል እውነት ነውና ጽኑ እያለ ለማጠናከሪያ ነው የሚነግራቸው የህይወቱን ታሪክ::
ከዚህ የህይወት ጉዞ ያየሁት:-
1. በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ እንደለየኝ
በጸጋውም እንደጠራኝ
2. ከስጋና ደም ጋር ሳልማከር መታዘዝን
3. ለእግዚአብሔር ስም መመስገን
ምክንያት መሆንን እንዳለብኝ
አይቻለሁኝ::
ጌታሆይ ተመስገን ስለመረጥከኝ ደግሞም እርዳኝ እንድታዘዝ የመታዘዝን መንፈስ በእኔ ውስጥ አድርግ:: በእርምጃዬም ሁሉ ለአንተ ምስጋና ይምጣ እንጂ ስምህ ከእኔ የተነሳ አይሰደብ:: በእየሱስ ስም! አሜን!
God bless you, sister Betty for sharing your insights on the Letter to the Galatians. I have found many important lessons in your writings. One of them is the Apostle Paul's commitment to preaching the Gospel without making any compromise. May God help all of us to faithfully preach and teach His Word, and to spreading the Good News of Jesus Christ.